ትንቢተ ሕዝቅኤል

We are a church that believes in Jesus Christ and the followers and This is where you should start.

ምዕራፍ 43

1 ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ።
2 ፤ እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር።
3 ፤ ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።
4 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ።
5 ፤ መንፈሱም አነሣኝ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
6 ፤ በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር።
7 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤
8 ፤ መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱም መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።
9 ፤ አሁንም ግልሙትናቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘላለም በመካከላቸው አድራለሁ።
10 ፤ አንተም የሰው ልጅ፥ ከኃጢአታቸው የተነሣ ያፍሩ ዘንድ ለእስራኤል ወገን ይህን ቤት አሳያቸው አምሳያውንም ይለኩ።
11 ፤ ከሠሩትም ሥራ ሁሉ የተነሣ ቢያፍሩ፥ የቤቱን መልክና ምሳሌውን መውጫውንም መግቢያውንም ሥርዓቱንም ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዓቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው።
12 ፤ የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ዳርቻው ሁሉ በዙሪያው ከሁሉ ይልቅ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።
13 ፤ የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፥ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው መሠረት እንዲሁ ነው።
14 ፤ በመሬቱም ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው።
15 ፤ ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት።
16 ፤ የምድጃውም ርዝመት አሥራ ሁለት ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው።
17 ፤ የእርከኑም ርዝመት አሥራ አራት ክንድ ወርዱም አሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ እኩል ክንድ ነው፥ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።
18 ፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው።
19 ፤ ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
20 ፤ ከደሙም ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹም በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ በዙሪያውም ባለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታስተሰርይለትማለህ።
21 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በታዘዘው ስፍራ ይቃጠላል።
22 ፤ በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል።
23 ፤ ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል።
25 ፤ ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።
26 ፤ ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹትማል፥ እንዲሁም ይቀድሱታል።
27 ፤ ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን የደኅንነትንም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Post navigation